በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር በአቶ ፍቅሬ አማን የተመራ የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች የልማት ፕሮጀክቶችን አፈጻጸም ያለበትን ደረጃ ለመጎብኘትና ከማኅበረሰቡ ጋር ትውውቅ እንዲሁም ውይይት ለማድረግ ኮንታ ዞን ጪዳ ከተማ ገብቷል።
ልዑኩ ጪዳ ከተማ ሲደርስ የኮንታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገዛኸኝ ገዝሙን ጨምሮ ሌሎች የዞኑና የጪዳ ከተማ አመራሮች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል
ልዑኩ በጪዳና አመያ ከተሞች የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶችን የሚጎበኝ ሲሆን፣ በነገ ዕለት በአመያ ከተማ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር የትውውቅና የጋራ ውይይት እንደሚያካሂድ ይጠበቃል።
የልማት ሥራዎች ጉብኝቱና ሕዝባዊ ውይይቱ በልማት፣ በሰላምና በመልካም አስተዳደር ዙሪያ የሚነሱ ጥያቄዎችን በቀጥታ ለማዳመጥና የጋራ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ያለመ ነው።
የክልሉ መንግሥት የመደመር መንግሥት ምሥረታን ተከትሎ ለሕዝቡ አንገብጋቢ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ተግባራዊ ምላሽ ለመስጠት ቅድሚያ ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
በዚህም ግንባታቸው የዘገየ ፕሮጀክቶችን በመገምገም፣ የአፈጻጸም ማነቆዎችን በመለየትና መፍትሔ በማስቀመጥ ሥራቸውን ለማፋጠን የተቀናጀ ጥረት ጀምሯል ።
በርዕሰ መስተዳድሩ ከተመሩ ልዑካን ቡድኖች መካከል የክልሉ መንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ተክሌ በዛብህ፣ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸውን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ አስተባባሪ አካላትና የቢሮ ኃላፊዎች ይገኙበታል ።




