በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል “ከልመና ወደ ብልፅግና” የመሻገርና አገራዊ ክብርን የማስጠበቅ ግብ በመሰነቅ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን የክልሉ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ገለጸ።
በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና በግብርና ሚኒስቴር ትብብር “ከተረጅነት ወደ ምርታማነት” በሚል መሪ ቃል በሐዋሳ ከተማ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
በዚህ መድረክ ላይ የተገኙት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ለማ መሰለ (ዶ/ር) ክልሉ ተረጂነትን ለማስቀረት እያከናወነ ስላለው ተግባር ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ክልሉ ያለውን ልዩ ተፈጥሯዊ ፀጋና አቅም በመለየት በተሰሩ ስራዎች፣ ከክልል ፍጆታ አልፎ ለአገር የሚተርፉ የግብርና ምርቶች እየተመረቱ ይገኛል።
በተለይም ቀደም ሲል በተረጂነት ሕይወት ውስጥ የነበሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ወደ ምርታማነት ለማሸጋገር በተደረገው ጥረት ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል።
የሥራው ዋነኛ ትኩረት ዜጎችን ከልመና ወደ ብልፅግና ማሻገርና የአገርን ክብር ማስጠበቅ መሆኑ ተመላክቷል።
በሐዋሳው የውይይት መድረክ ላይ የፌዴራል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የሲዳማ፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች የሥራ መሪዎችም ተገኝተው በተመሳሳይ የየክልሎቻቸውን ተሞክሮ አጋርተዋል።




