በምርጫ ወቅት የፖሊስ ሚናና ስነምግባር በሚል ርዕሰ ጉዳይ በካፋ ዞን ለሚገኙ የፖሊስ አባላት በቦንጋ ከተማ ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል ።
በመድረኩ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት በክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የመረጃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ረዳት ኮሚሽነር በላይነህ በቀለ ለ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ተሳተፊ የሚሆኑ የጸጥታ አካላት ሚናቸውንና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መረዳትና ማወቅ ይገባቸዋል ብለዋል።
ይህም ምርጫው በሠላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅና የፖሊስ አባላት ስነምግባርን በጠበቀ መልኩ ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ እንደሚያስችል ገልጸዋል።
በተለይ የህዝቡን ሠላምና ደህንነት ባስጠበቀ መልኩ ምርጫው እንዲከናወን ማድረግ የጸጥታው አካላት ኃላፊነት መሆኑንም ረዳት ኮሚሽነሩ አሳስበዋል።
በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት ውስጥ ስልጣን በምርጫ ብቻ እንደሚገኝ የገለጹት ረዳት ኮሚሽነሩ ምርጫ ሂደቱም ህዝቡ የመምረጥ ስልጣኑን የሚለማመድበት መድረክ ነው ብለዋል።
በመሆኑም የጸጥታው አካል የህዝቡን ደህንነትና ሠላም ከማስጠበቅ ባሻገር በምርጫ ስልጣን የያዘውን መንግስት የማገልገል ህገ መንግስታዊ ኃላፊነት እንዳለበት መገንዘብ እንደሚገባም አሳስበዋል።
በመድረኩም በምርጫ ወቅት የጸጥታ አካላት ሚናና ስነምግባር በሚል ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ የስልጠና ሰነድ በካፋ ዞን ፖሊስ አዛዥ በኢንስፔክተር ዳዊት ደሳለኝ እየቀረበ ሲሆን የካፋ ዞንና የቦንጋ ከተማ አስተዳደር መዋቅር የፖሊስ አባላት እየተሳተፉ ይገኛል።




