ማንኛውም ሀገራዊ ሽግግር እና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ስኬታማ ሊሆን የሚችለው፣ ሂደቱን የሚመሩ አካላት የኃላፊነት ወሰንን በተመለከተ በኅብረተሰቡ ዘንድ የተሟላ ግንዛቤ እና ግልፅነት ሲፈጠር ብቻ ነው።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ሀገራዊ ምክክር የነገዋን የበለፀገች ሀገራችንን በጽኑ መሠረት ላይ ለመገንባት ያለመ ነው።

የዚህን ታላቅ መድረክ ስኬታማነት ለማረጋገጥ ታዲያ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑን የኃላፊነት ወሰን እና ሚና በማብራራት አንዳንድ የተሳሳቱ ግንዛቤዎችን ማረም ይገባል።

በተወሰኑ አካላት ዘንድ የሚስተዋለው ዋነኛው የተሳሳተ ግንዛቤ፣ ኮሚሽኑን እንደ አንድ የመጨረሻ “የፖለቲካ ውሳኔ ሰጪ” ወይም “ሕግ አውጪ” አካል አድርጎ ማየት ነው።

እውነታው ግን፣ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ራሱን ችሎ የፖለቲካ ውሳኔዎችን የሚያሳልፍ ተቋም አይደለም።

ይልቁንም የተቋሙ ኃላፊነት፥ በገለልተኝነት የምክክር መድረኮችን ማመቻቸት፣ ልዩነቶች የሚቀራረቡበትን ድልድይ መፍጠር እና ሂደቱን ለህዝብ ይፋ ማድረግ ነው።

ኮሚሽኑ የራሱን የመፍትሔ አቅጣጫ የሚያስቀምጥ ሳይሆን የሕዝቡ ድምፅ በነፃነት የሚደመጥበትን መድረክ የሚያዘጋጅ ታማኝ አመቻች ነው።

በአንፃሩ፣ የዚህ ታሪካዊ የምክክር ሂደት ትክክለኛ የሃሳብ አመንጪዎች የሆኑት የንዑሳን ቡድኖች ሚና ሊሰመርበት ይገባል።

እነዚህ ንዑሳን ቡድኖች የልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን እና የባለሙያዎችን ድምፅ ይዘው የሚቀርቡ የውይይቱ ዋነኛ ሞተሮች ናቸው።

ሚናቸውም፣ የትኛውንም ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ልዩነት ሳይፈሩ እና ሳያቅማሙ የውይይቱን መነሻ ሃሳቦች በነፃነት ማመንጨት እንዲሁም የመፍትሔ አማራጮችን ማቅረብ ነው።

የንዑሳን ቡድኖቹ ሃሳብ በነፃ ውይይት ይበልጥ በዳበረ ቁጥር፣ ምክክሩ ወደ እውነተኛ እና ዘላቂ ሀገራዊ መግባባት የሚያመራበትን መዋቅራዊ ጥንካሬ ይጎናጸፋል።

በኮሚሽኑ ተለይተው የቀረቡት ስምንቱ ዋና ዋና አጀንዳዎች ኅብረተሰቡ ሁሌም በቀዳሚነት ሊያተኩርባቸው የሚገቡ የምክክሩ መዋቅራዊ ማዕቀፍ ናቸው።

በተመካካሪዎች የላቀ ተሳትፎ በእነዚህ አጀንዳዎች ላይ በጥልቀት በመወያየት የጋራ አቋም መያዝ የሕልውና ያህል ወሳኝ ጉዳይ ነው።

ምክክሩ የትውልዶችን የዘመናት ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ የመመለስ እና ታሪካዊ ስብራቶቻችንን የመጠገን ታላቅ ኃይል አለው።

በመሆኑም በሂደቱ የተመካካሪዎች ሙሉ ቁርጠኝነት እና የላቀ ተሳትፎ ለብሔራዊ መግባባታችን ዋስትና ነው፤ ልዩነቶቻችንን ወደ ጋራ ጥንካሬ በመቀየር የሀገራችንን ብሩህ ተስፋ እና ህልውና ለማረጋገጥ ያስችለናል።

0 0 votes
Article Rating
Subscribe
Notify of
guest
0 Comments
Oldest
Newest Most Voted
Inline Feedbacks
View all comments
0
Would love your thoughts, please comment.x
()
x