በታርጫ ከተማ ሲካሄድ የቆየው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክር ቤትና የዞን ምክር ቤቶች የ2019 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ተጠናቋል።
በግምገማ መድረኩ የምክር ቤቶችን የሥራ አፈጻጸም በመገምገም የታዩ ጉድለቶችን ማረም፣ የተሻሉ ተሞክሮዎችን ማስፋፋትና በቀጣይ ሩብ ዓመት የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚገባ ተገልጿል።
የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ወንድሙ ኩርታ በቀረቡት ሪፖርቶች ላይ በሰጡት አስተያየት፣ ምክር ቤቶች የሕዝብ ድምፅ እንደመሆናቸው የአስፈጻሚ አካላትን ዕቅድና አፈጻጸም በቅርበት በመከታተልና በመገምገም ልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በተለይም በቀበሌ ደረጃ የምክር ቤት ጉባኤዎችን በአግባቡ ማካሄድ፣ ከሕብረተሰቡ የሚነሱ ጉዳዮችን በመወያየት የመፍትሔ አቅጣጫ ማስቀመጥና ተጠያቂነትን ማጠናከር የምክር ቤቶች ቁልፍ ተግባር መሆኑን ጠቁመዋል።
እንዲሁም የሚወጡ ሕጎችና አዋጆች በተግባር ላይ መዋላቸውን መከታተል፣ የኦዲት ግኝት እርምጃዎችን ማረጋገጥ፣ ያሉ የሕዝብ ቅሬታዎችን በዕቅድ ውስጥ በማካተት መፍትሔ መስጠትና ሪፖርቶችን በቼክሊስት መሠረት ማቅረብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በቀጣይ ሩብ ዓመት በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ያልተሳኩ ተግባራትን ለማካካስ፣ የመስክ ምልከታ ሥራዎችን በተጨባጭ ውጤት ለማጀብና በምክር ቤቶች መካከል ያለውን ቅንጅታዊ አሠራር ለማጠናከር በትኩረት መሥራት እንደሚገባም አመልክተዋል።
የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፀሐይ ደርጫ በበኩላቸው፣ ምክር ቤቶች ሕዝቡ በምርጫ ካርዱ የሰጣቸውን አደራ በተግባር በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
በሕዝቡ ዘንድ የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት በሙሉ አቅም መሥራት እንደሚገባ ያስገነዘቡት ወ/ሮ ፀሐይ፣ ተግባራትን በማንጠባጠብና ምክንያቶችን በመደርደር የሚጠበቀውን ውጤት ማስመዝገብ እንደማይቻል ጠቁመዋል።
በተለይም በቀበሌ ደረጃ የምክር ቤት ጉባኤዎች በአግባቡ እንዲካሄዱ፣ በሥራ አፈጻጸም የታዩ ጉድለቶች እንዲታረሙና የተቀመጡ ተልዕኮዎች በውጤት እንዲታጀቡ በቅንጅትና በቁርጠኝነት መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የምክር ቤቶች ፎረም ምርጥ ተሞክሮዎችን ለመቀመር፣ ልምድ ለመለዋወጥና የሥራ አፈጻጸምን ለማሻሻል ያለው ሚና ጉልህ በመሆኑ መድረኩ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ገልጸዋል።
በመድረኩ የተሳተፉ የተለያዩ ደረጃዎች ምክር ቤት አፌ ጉባኤዎችና የቋሚ ኮሚቴ አባላት የሥራ አፈጻጸም ጉድለቶችን በማረም፣ የሚወጡ ሕጎችና አዋጆች ተፈጻሚነትን በመከታተልና በሁሉም ዘርፎች ተጨባጭ ውጤት በማስመዝገብ ለሕዝብ ተጠቃሚነት እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።
የግምገማ መድረኩ በ2019 በጀት ዓመት ቀሪ ወራት የምክር ቤቶችን አፈጻጸም ለማሻሻል፣ የታዩ ክፍተቶችን ለማረምና የሕዝብ ጥቅምን የሚያረጋግጡ ተግባራትን በተሻለ ደረጃ ለማከናወን አቅጣጫ ያስቀመጠ መሆኑ ተገልጿል።




