የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ከዳውሮ ህዝብ ጋር በታርጫ ከተማ እየመከሩ ነው።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ፍቅሬ አማን በመድረኩ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፤ የመደመር መንግስት ባለፉት አመታት የክልሉን ህዝቦች የልማትና ዴሞክራሲ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል።
በተጨማሪም የአካባቢውን ፀጋ በመጠቀም የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እየተደረገ የሚገኘው ጥረት አበረታች መሆኑን ጠቅሰው፤ ያለውን ፀጋ ወደ ተጨባጭ ለውጥ ለመቀየር የጋራ ርብርብ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
የክልሉ መንግስት ከዞኑ ህዝብ ጎን እንደሚቆምና አመራሩ በአገልጋይነት መንፈስ ተግባሩን እንደሚያከናውንም ርዕሰ መስተዳድሩ አረጋግጠዋል።
የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ትዕዛዙ ባዩ በበኩላቸው ህዝቦች ለዘመናት ምላሽ ተነፍገው የቆዩበት ስርዓት ተወግዶ በለውጡ መንግስት የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ እየተሰጠባቸው መሆኑን ገልፀዋል።
ለዚህም ማሳያ በዞኑ የመንገድ መሠረተ ልማት፣ የንፁህ መጠጥ ውሃና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት መስፋፋትን እንደ አብነት ጠቅሰዋል።
የክልሉ መንግስት በሚያስቀምጠው አቅጣጫ መሠረት በዞኑ ህዝብ የነቃ ተሳትፎ በቀጣይ የልማት ስራዎችን ለማሳለጥ እንደሚሰሩም ቃል ገብተዋል።




