“ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ ቃል ክልላዊ የአንድ ጀምበር አረንጓዴ አሻር መርሐ-ግብር በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቤንች ሸኮ ዞን ደቡብ ቤንች ወረዳ ገሊት በይፋ ተጀምሯል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በማስጀመሪያ መርሐግብር ባስተላለፉት መልዕክት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የመደመር መንግስትና የብልጽግና ፓርቲ የአየር ሚዛን መጠበቂያ ትልቁ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የዓለም አየር ሚዛን ከመጠበቅ ባሻገር ጥምር ግብርና እና የአትክልት ልማት ስራዎች ያካተተ በመሆኑ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ከፍተኛ ፋይዳ አለው ብለዋል።
በክልል ደረጃ 25 ሚሊዮን ችግኞች በአንድ ጀምበር የሚተከሉ መሆናቸውን የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ በአገር አቀፍ ደረጃ 800 ሚሊዮን ችግኞች በአንድ ጀምበር ይተከላሉ ብለዋል።
አረንጓዴ አሻራ በአንድ ጀምበር ተተክሎ የሚተው ሳይሆን በዘላቂነት የሚቀጥል ተግባር በመሆኑ በተጀምረው መንገድ አጠናክሮ ማስቀጠል እና የተተከሉትን ችግኞች የመንከባከብ ስራ በስፋት ሊሰራ እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።
መላው የክልሉ ማህበረሰብ ክፍል ይህ አገራዊ ተልዕኮ የተሳካ እንዲሆን በክልሉ የተዘጋጁ የተከላ ጉድጓዶች እስኪጠናቀቁ የተከላ ስራው ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
የቤንች ሸኮ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን መንገሻ በበኩላቸው አረንጓዴ አሻራ ለዞኑ ማህበረሰብ የስነ-ምህዳር ጥበቃ እና የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
በዞኑ የአትክልትና የፍራፍሬ ልማት ስራም በስፋት የሚከናወንበት በመሆኑ ተግባሩ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል።
የደቡብ ቤንች ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተሾመ ኪያስካ በበኩላቸው ሀገራዊ አረንጓዴ አሻራ ለአርሶአደሩ ምርትና ምርታማነት ከፍተኛ ፋይዳ ያለው በመሆኑ ተግባሩ በወረዳው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።




