የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መንግስት የሕዝቡን የልማት ፍላጎት ለማሳካትና የክልሉን የማንሰራራት ጉዞ እውን ለማድረግ የሚያስችል የአመራር ምደባና የመንግስት ምስረታ ሥራ ማከናወኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ፍቅሬ አማን ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉን መንግስት ምስረታና ተያያዥ ጉዳዮች አስመልክተው ለሚዲያ አካላት በሰጡት የፕሬስ ኮንፈረንስ መግለጫ፣ የመደመር መንግስት ኢትዮጵያን የአፍሪካ ተምሳሌት ለማድረግ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የክልሉ መንግስትም የተያዘውን አገራዊ አቅጣጫ በመከተልና የክልሉን የማንሰራራት ዘመን እውን ለማድረግ የሚያስችሉ የልማት ስትራቴጂዎችን በመተግበር እንደሚሰራ አስረድተዋል።
የአመራር ምደባውና የመንግስት ምስረታው የአመራር ውጤታማነትን፣ የሙያ መስመርን፣ የትምህርት ዝግጅትንና አካታችነትን መሠረት በማድረግ መከናወኑን የገለጹት አቶ ፍቅሬ፣ የተመደቡ አመራሮች የሕዝብና የመንግስት አደራቸውን በቁርጠኝነት መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ከክልሉ ምስረታ ጀምሮ ሕዝቡ ለልማትና ለክልሉ ግንባታ እያደረገ ያለው ተሳትፎ የሚደነቅ መሆኑን በመጥቀስ፣ ይህንን የሕዝብ አቅምና የክልሉን እምቅ ጸጋ በማቀናጀት የክልሉን ማንሰራራት ማረጋገጥ ከአመራሩ የሚጠበቅ ዋነኛ ኃላፊነት መሆኑን አመልክተዋል።
በሌላ በኩል፣ የመደመር መንግስት እየተከተለ ያለው የፌዴራሊዝም ሥርዓት ክልሎች ያላቸውን የተፈጥሮ ሀብትና ጸጋ በአግባቡ እንዲጠቀሙ ሰፊ ዕድል የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል። በመሆኑም የክልሉን የማዕድንና ሌሎች ሀብቶች በአግባቡ በመምራትና በማስተዳደር ወደ ተጨባጭ የልማት ውጤት መቀየር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የክልሉን የልማት አቅም ወደ ተጨባጭ ሀብት ለመቀየር በተለያዩ ዘርፎች ሰፊ ዕቅዶች መያዛቸውን ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል። በክልሉ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ፣ በመካከለኛ ደረጃ ያሉ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን ለማስቀጠልና አዳዲስ ሥራዎችን ለማስጀመር በትኩረት እንደሚሰራ አመልክተዋል።
በከተሞች ልማት ዘርፍ ብዝሃ ከተማነትን ለማጠናከር፣ በከተሞች የሚከናወኑ የኮሪደር ልማት ሥራዎችን ለማስፋፋትና ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ እንዲሆኑ ከማድረግ ባለፈ የቱሪዝም መዳረሻነታቸውን ለማጎልበት እንደሚሰራ ገልጸዋል። በከተሞች የሚካሄዱ የክልል ቢሮዎች ግንባታ ሥራዎችም በጥልቀት ተገምግመው በመጠናቀቅ ላይ ያሉት በፍጥነት እንዲጠናቀቁ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
በግብርና ዘርፍ ደግሞ ሰፊውን የአርሶ አደርና የአርብቶ አደር ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ የግብርና መካናይዜሽንን ማስፋፋት፣ የኩታ ገጠም እርሻን ማጠናከርና የቴክኖሎጂ ስርጸትን ማሳደግ ትኩረት የሚሰጣቸው መሆኑን ጠቁመዋል። በተለይም በቡና፣ በሻይና በቅመማ ቅመም ምርቶች ላይ በመሥራት የክልሉን የምርት አቅምና የገቢ ምንጮች ለማሳደግ ዕቅድ መያዙን አስረድተዋል።
በተጨማሪም የክልሉን እምቅ ጸጋ ወደ ተጨባጭ ሀብት ለመቀየር 16 የልማት ፓኬጆች ተቀርጸው በተግባር ላይ እየዋሉ መሆናቸውን ጠቁመው፣ በክልሉ ሀብት ላይ የተመሠረቱ ኢኒሼቲቮችን በማጠናከር የሚጠበቀውን ውጤት ለማምጣት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በየደረጃው ከሚገኙ ወጣቶች ጋር የውይይት መድረኮችን በማካሄድ፣ የክልሉን ሀብት መሠረት ያደረገ የሥራ ዕድል ፈጠራን በማስፋፋትና ወጣቶች ከልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በትኩረት እንደሚሰራ ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።
በአርብቶ አደር አካባቢዎች አልፎ አልፎ የሚከሰቱ የጸጥታ ችግሮችንም ማኅበረሰቡን ባሳተፈ መንገድ በመፍታት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እንደሚሰራ ገልጸው፣ በዚህ ረገድ የአመራሩ ሚና ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በሰብዓዊ ድጋፍ ዘርፍም ክልሉ የሚያጋጥሙትን የድጋፍ ፍላጎቶች በራሱ አቅም መሸፈን እንዲችል እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን ወደ ተጨባጭ ውጤት በመቀየር በቅርቡ የራስ አቅም የሰብዓዊ ድጋፍ ሥርዓትን ይፋ ለማድረግ እንደሚሰራ አመልክተዋል።
የመንግስትን አገራዊ አቅጣጫ በመከተል ሙስናንና ብልሹ አሠራሮችን ለመቅረፍ የዲጂታል መንግስት አገልግሎት አሰጣጥን የማጠናከር ሥራ እንደሚቀጥል ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል። ከዚህ ጎን ለጎን በሙስናና በብልሹ አሠራር ላይ ጠንካራ እርምጃ እንደሚወሰድም አስታውቀዋል።
አቶ ፍቅሬ አማን በመግለጫቸው መጨረሻ፣ የክልሉን የማንሰራራት ጉዞ ለማረጋገጥ የክልሉ መንግስትና በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች በትጋትና በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ገልጸዋል። ሕዝቡም ከአዲሱ መንግስት ጎን በመቆም ለክልሉ ልማት፣ ሰላምና ዕድገት የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።




