የማዕድን ሀብት ክልሉ ካለው የተፈጥሮ ሀብት ዋነኛው እና በሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ዕድገት ላይ የድርሻውን እየተወጣ ያለ ዘርፍ በመሆኑ ዘርፉን ማዘመንና በአግባቡ ማስተዳደር እንደሚገባ ርዕሰመስተዳድር አቶ ፍቅሬ አማን ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉን መንግስት ምስረታ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ለሚዲያ አካላት በሰጡት የፕሬስ ኮንፈረስ መግለጫ ክልሉ ያለውን እምቅ ጸጋ በአግባቡ መጠቀም እንዲችል የሚያደርግ የአመራር ምደባ መደረጉን ተናግረዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ የመደመር መንግስት እየተከተለ ያለው የፌዴራሊዝም ስርዓት ክልሎች በነፃነት ያላቸውን ሀብት እና የተፈጥሮ ጸጋ በነፃነት የሚጠቀሙበትን ሰፊ ዕድል የፈጠረ በመሆኑ ማዕድንና ሌሎች ሀብቶችን በተገቢው መንገድ መምራትና ማስተዳደር ይገባል ብለዋል።
የአርብቶአደሩ አካባቢ ሰፊ የማዕድን ሀብት ያለበት አካባቢ በመሆኑ አልፎ አልፎ የሚስተዋለውን የጸጥታ ችግር ሙሉ በሙሉ በመቅረፍ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ የልማት ስራዎችን ለማከናወን የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝም አቶ ፍቅሬ አመላክተዋል።
በማዕድን ዘርፍ የተጀመረውን የኢንቨስትመንት ልማት በማስፋት እና ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ በማላቅ የክልሉን ብሎም የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በማሳደግ ለክልሉ ማንሰራራት ዘመን እውን ለማድረግ በሚደረግ ጥረት ውስጥ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣም ርዕሰመስተዳድሩ አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።




